የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የኢትዮጵያ መብራት ኃይልን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ሐሙስ ፣ነሐሴ 16 ቀን ፣ 2016 ዓ.ም በኃይሌ ግራንድ ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገመገመ፡፡
በግምገማው የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱ፣ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ግንባታ 96.7 በመቶ የደረሰ መሆኑ፣ በውጭ የኃይል ሽያጭ ከታንዛኒያ ጋር ስምምነት መደረሱ፣ ወቅታዊ ሂሣብ በውጭ ኦዲት የተመረመረ መሆኑ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት ካለፉት ዓመታት ዕድገት ማሳየቱ እንዲሁም የስጋት አስተዳደር ትግበራ መሻሻሉ በበጎ ጎን የተነሱ ተግባራት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ በኤሌክትሪክ ኃይል ምርት አፈጻጸም 20,523 ጌጋ ዋትስ ኃይል ያመነጨ ሲሆን፣ ይህ የዕቅዱን 97.8 በመቶ እና ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት አፈጻጸም ደግሞ በ15.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የ19,086 ጌጋ ዋትስ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ በማከናወንም የዕቅዱን 100 በመቶ አሳክቶ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት በ18 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ በግምገማው ታይቷል፡፡
የኤሌትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ በተያዘ ዕቅድ መሰረትም የማስተላለፊያ መስመርን ለአገልግሎት ዝግጁ ከማድረግ እና በፍተሻና አስቸኳይ ጥገና ክስተቶች ምላሽ የመስጠት ሥራዎች የዕቅዱን 90.3 በመቶ አሳክቷል፡፡ በሀገር ውስጥ ሽያጭ ብር 20 ቢሊዮን እንዲሁም በውጭ ሀገር ሽያጭ ደግሞ 113 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘትም ችሏል፡፡ በተያዘ ዕቅድ መሰረት ድርጅቱ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፣ የብር 24 ሚሊዮን ወጪ መቀነስ ችሏል፡፡ በማህበራዊ አገልግሎት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የብር 17.4 ሚሊዮን ድጋፍ አድርጓል፤ ለ4,364 ዜጎች ደግሞ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡
የግምገማ መደረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ሲሆኑ፣ ግምገማው በኦፕሬሽንና ፋይናንስ፣ በኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ በፕሮጀክትና ሪፎርም ዕቅድ አፈጻጸሞች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በግምገማው በበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም የታዩ መሻሻሎችና ክፍተቶች ተገምግመው በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገባ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ተሰጥታል፡፡