የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሆልዲንግና አስተዳደር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን ግንቦት 24 ቀን 2024 በሂልተን ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ የልምድ መጋራት ስልጠና ሰጥተዋል።
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን አመራሮች ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ የልምድ ልውውጥ ስልጠና ሰጠ፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በባለስልጣኑ መቋቋም ሂደት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን፣ ባለስልጣኑ ወደተግባር ሲገባ የበለጠ ውጤታማ ሊያደርጉት የሚችሉ ልምዶችን አስተዳደሩ እንዲያካፍለው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ስለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ታሪካዊ ዳራ፣በልማት ድርጅቶች የአፈጻጸም አስተዳደር(performance management)፣በኦፕሬሽን እና የፋይናንስ አፈጻጸም ቁልፍ አመላካቾች(KPIs) እና በኮርፖሬት ገቨርናንስና ፋይናንስ አተገባበር ላይ ያተኮረና ተግባር ተኮር የሆነ ስልጠና ለባለስልጣኑ አመራሮች ተሰጥቷል፡፡
የልምድ ልውውጥ ስልጠናውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ያስጀመሩ ሲሆን፣ሀገሪቱ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዳሏትና ለሀገር ልማትም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርም ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የልማት ድርጅቶች አመራርና አሰራር ሥርዓት ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ እንደሆነ የገለጹት ዋና ደፋይሬክተሩ አስተዳደሩ እንደዚምባብዌ ላሉ ሀገራትም ልምድ ማካፈሉን ፣ ባለስልጣኑ ሰፊ ልምድ ካካበተው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር አጋዥ የሆነ ልምድ እንደሚያገኝ እና በቀጣይም አስተዳደሩ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው የልማት ድርጅቶችን ባህሪ ከማጥናት ጀምሮ ፣የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችንና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን፣ የልማት ድርጅቶችን የሚመራ አካል ከድርጅቶቹ ቦርድ እና ማኔጅመንት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት፣የድጋፍና ክትትል ተግባራት በምን መልኩ ሊከናወኑ እንደሚገባ ፣ ስለዕቅድ ዝግጅት፣ ግምገማና ግብረመልስ ሥርዓቶች፣የኮርፖሬት ገቨርናንስና ፋይናንስ ሥርዓቶችን ለመዘርጋት መከናወን ስላለባቸው ተግባራትና አፈጻጸማቸው፣የዓለምአቀፍ ሂሳብ ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት(IFRS) አተገባበርን ጨምሮ የልማት ድርጅቶችን በመምራት ሂደት ሊያግዙ የሚችሉ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የባለስልጣኑ አመራሮችም ስልጠናው የልማት ድርጅቶችን ለመምራት በሚያደርጉት ዝግጅት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ከባለስልጣኑ አመሰራረት ጀምሮ ላደረገው አስተዋጽኦ ያላቸውን ምስጋና አቅርበው በቀጣይ ለሚያስፈልጉ ድጋፎችም አስተዳደሩ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ባለስልጣኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲመሩና ከራሳቸው ባለፈ ለከተማ አስተዳደሩና ለህብረተሰቡ ልማት ድጋፍ እንዲሰጡ ለማድረግ በቅርቡ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡