የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ለ52 ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ለአንድ ዓመት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቀቀ::
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ፣መንግሥት ከግል አልሚዎች ጋር በጋራ ልማት ለሚያለማቸው ድርጅቶች፣ ለክልል እና ለከተማ አስተዳደር የልማት ድርጅቶችና ኢንዶውመንት አመራሮች ፣ለቦርድ አባላት እና ባለሙያዎች ከሰኔ 09 ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 05 ቀን 2015 ዓ.ም ለአንድ ዓመት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ሐምሌ 05 ቀን 2015 ዓ.ም ተጠናቀቀ፡፡
በመዝጊያ ስነሥርዓቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ አስተዳደሩ የተቋቋመባቸውን ዋና ዋና ዓላማዎች ጠቅሰው አስተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ 11 የኮርፖሬት አስተዳደርና 4 የኮርፖሬት ፋይናንስ መመሪያዎችን በማዘጋጀት በልማት ድርጅቶቹ ተፈጻሚ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ/ Agency of France Development (A.F.D)/ እና ስልጠናውን ከሰጠው ከፍራንክ ፈርት የፋይናንስና ማኔጅመንት ትምህርት ቤት /Frankfurt School of Finance & Management/ ጋር ስልጠናው በጥሩ ሁኔታ እንዲካሔድ በጋራ በመስራታችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡
ስልጠናው የልማት ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ትርፋማ እንዲሆኑ የሰው ኃይል አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ 21 ርዕሶችን በጥናት በመለየት ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠ ነው፡፡ በወጣ ግልጽ ጨረታ መሰረት አሸናፊ የሆነው የፍራንክ ፈርት የፋይናንስና ማኔጅመንት ትምህርት ቤት ደግሞ ከአውሮፓ፣ከአፍሪካ እና ከአሜሪካ በተመረጡ አሰልጣኞች ስልጠናውን ለአንድ ዓመት ሰጥቷል፡፡
በመዝጊያ ሥነስርዓቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋ ፣የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ፣ የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቫሌሬ ቴሂኦ(Valérie Tehio)፣የፍራንክ ፈርት የፋይናንስና ማኔጅመንት ትምህርት ቤት ዳይይክተር አርዳክ ሙሰታፊና(Ardak Mustafina) እንዲሁም ከፍራንክፈርት የፋይናንስና ማኔጅመንት ት/ቤት ፕሮፌሰር ዶ/ር አዶ ሰቲፈንስ (Prof.Dr. Udo Steffens) ተሳትፈዋል፡፡