ለአስተዳደሩ ተጠሪ ከሆኑ አስር የልማት ድርጅቶች መካከል የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ተገመገመ፡፡
የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ በመረከብ ከኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ የሚመደብለትን ካፒታል፣ ከንግድ ሥራ እንቅስቃሴ የሚያገኘውን ገቢ እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች የሚመደብለትን ገንዘብ በመጠቀም የተረከበውን ዕዳ መክፈል፣ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል የሚተላለፉ እንዲሁም የሚፈርሱ የመንግስት ልማት ድርጅቶችን ንብረት እና ዕዳ በመረከብ የማጣራትና የማስተዳደር እና ሌሎች ተግባርና ኃላፊነቶችን ይዞ የተቋቋመ ኮርፖሬሽን ነው፡፡
ከተቋቋመበት ከየካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት እየሰራ ይገኛል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመትም የብር 6.8 ሚሊዮን ጠቅላላ ገቢና የብር 3.7 ሚሊዮን ትርፍ አስመዝግቧል፡፡በኮርፖሬት ማህበራዊ አገልግሎትም ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የብር 400 ሺህ ድጋፍ አበርክቷል፡፡ከባለአደራ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ከተረከባቸው ከወለድ፣ ከህንጻ ኪራይ እንዲሁም ከሌሎች በድምሩ ብር 3.92 ሚሊየን ገቢ ያገኝ ሲሆን ፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ንብረቶችን በማሰባሰብና በማደራጀት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ ይገኛል፡፡የኮርፖሬሽኑን ሂሳብ ወቅታዊ ማድረግ ተግባርም ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል፡፡የኮርፖሬሽኑ የህንጻ ዕድሳት ደረጃም በአስተዳደሩ አመራሮች ተጎብኝቷል።
በዕለቱ ሌላው የተገመገመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሲሆን፣በሩብ ዓመቱ በወጪ ንግድ፣ በተኪ ምርቶች፣በሼድ መያዝ ምጣኔ ፣ባለሀብቶችን በመሳብ ፣የለማ መሬት በመያዝና በመጠቀም ምጣኔ እና በንግድ ትስስር አበረታች አፈጻጸሞችን ማስመዝገቡ ታይቷል፡፡ በዚህ መሰረትም በሩብ ዓመቱ ሼዶች የመያዝ ምጣኔ 86 በመቶ ማድረስ ተችላል፡፡ በወጭ ንግድ የ26 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣የ53.3 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የተኪ ምርት ተመርቷል፡፡በሩብ ዓመቱ የ38 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ የምርት ትስስር በአምራቾችና በግብዓት አቅራቢዎች መካከል እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሩብ ዓመቱ ብር 865 ሚሊዮን ጠቅላላ ገቢ በማግኘት፣የብር 295 ሚሊዮን ትርፍ ከታክስ በፊት አስመዝግቧል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ ደግሞ በሩብ ዓመቱ ለ12,683 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡የኮርፖሬት ማህበራዊ አገልግሎት አንዱና መልካም አፈጻጸም የታየበት ሲሆን ፣ የትምህርት ቤት ግንባታን ጨምሮ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የብር 33.3 ሚሊዮን ድጋፍ ማድረግ ችሏል፡፡
በግምገማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ተወካይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋን እና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ትዕግስቱ አምሳሉን ጨምሮ የኮርፖሬሽኖች አመራሮች፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች እና ከአስተዳደሩ ኮርፖሬሽኖችን የሚከታተሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡