የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በአስተዳደሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝደንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ናቸው፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል አስተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ እንደመሆኑ መጠን የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የአመራር ልማት ተግባራት እንደሚያስፈልጉ፣ ድርጂቶቹም አሁናዊ እና ቀጣይ ዓለማቀፍ ሁኔታዎችን በመገንዘብ ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር እራሳቸውን እያዩ እንዲሄዱ እንዲሁም የላቀ ውጤት ያመጡ ተቋማት እንዲበረታቱ ማድረግ ላይ ያተኮሩ የአመራር ልማት፣የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማበረታቻ ሥርዓቶች ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አስተዳደሩና የልማት ድርጅቶች የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑና የሀገርን ዕድገት ለመደገፍ የሚካሔድን ጥረትም ለመደገፍም እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው በአስተዳደሩና በልማት ድርጅቶቹ ጥረት በኪሳራ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ወደትርፋማነት መምጣታቸውን አስታውሰው ፣ በልማት ድርጅቶቹ ስለሚመጡ አፈጻጸሞች አካዳሚው የባለቤትነት መንፈስ እንደሚሰማው ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አካዳሚው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ፣አህጉራዊና ሀገራዊ ድርጅቶች ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በልማት ድርጅቶች ትልቅ ለውጥ ስለመኖሩና ይህ ለውጥ ደግሞ የበለጠ ተደግፎ ወደትውልድ ሊተላለፍ እንዲችል በአመራር ልማት መደገፍ አለበት ብለዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ሁለቱም ተቋማትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በጥናትና ምርምር፣በአመራር ልማት ፕሮግራሞች፣በማማከር እና በሌሎች አገልግሎቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡